00:00
መስከረም 24፣2017
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ አብዛኞቹ ተማሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ የመጣውን የኑሮ ጫና ተቋቁመው መማር እየተሳናቸው መሆኑና አንዳንዶቹም ለከፋ የአእምሮ ጤና ችግር መዳረጋቸው ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
አብዛኞቹ በዚህ መንገድ የሚማሩ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲዎችና በሌላውም የትምህርት ደረጃ የሚያስተምሩና በመንግስት የሶስተኛ ዲግሪ(PhD) ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የትምህርት እድል ተሰጥቷቸው ከአራቱም የኢትዮጵያ ጫፍ መጥተው ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀላቀሉ ናቸው፡፡
እነዚህ ተማሪ መምህራን ለሚያስተምሩበት ደረጃ በመንግስት የሚከፈላቸው ደመወዝ ከ11,000 ብር ያልበለጠ ነው፡፡
ምንም እንኳን የትምህርት ወጪያቸው በመንግስት ቢሸፈንላቸውም በኢትዮጵያ ባለው የኑሮ ውድነት በሚያገኙት በዚህ ደመወዝ ቤተሰብና ልጆቻቸውን ደጉመው፣ ቤት ተከራይተውና የምግብ ወጪያቸውን ሸፍነው መማር እንደተሰናቸው ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ዩንቨርሲቲዎች ያለ ቢሆንም አሁን ካለው የኑሮ ጫና ጋር ተደማምሮ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በሚማሩት ላይ ያይላል፡፡
የPhD ተማሪዎቹ የሚያገኙትን አብዛኛውን ደመወዝ ለቤተሰቦቻቸው ልከው የምግብ እንኳን ስለሚያጡ እስከ መራብ የሚደርስ ችግር ውስጥ መሆናቸውንና ተምረው ተምረው ዶክተር ከመባላቸው በፊት በተስፋ መቁረጥ ለአእምሮ ህመም ጭምር እየተዳረግን ነው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ከ66 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞቹ ባሻገር 72 በሚደርሱ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞቹ በአሁኑ ወቅት 1,733 የፒ ኤች ዲ ተማሪዎች አሉት፡፡
Comments
00:00