00:00
ሐምሌ 17፣ 2016
ሕወሀት ዳግም ተመዝግቦ ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው ዋጋ እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
“እኔ ብፈልግም ባልፈልግም ምርጫ ቦርድ ሕወሃትን ካልተቀበለው ፓርቲው ዋጋ የለውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው፡፡
ከትንሳኤ 70 እንደርታ ፓርቲ ተወክለው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከበደ አሰፋ የተባሉ የፓርቲው አባል “ሕወሃት ከልክ በላይ ወደ ዝርፊያ ገብቷል፣ አይበቃም ወይ” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“ሕወሃት በወርቅ ፣ በማዕድን እና በተለያዩ የብረታ ብረት ዝርፊያ ላይ ተሰማርቶ እራሱን እያጎለበተ በማን አለብኝነት ጉባኤ እንዳናደርግ የሚከለክለን ምድራዊ ሀይል የለም እያለ መግለጫ እያወጣ እንደ ትናንትናው ወደ ፉከራ እየገባ ነው” ብለዋል፡፡
“የጊዜያዊ አስተዳደሩ መከለስ የለበትም ወይ” ሲሉም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
“ሕወሃት ትጥቅ ፈትቶ የፌዴራል የፀጥታ አካላት ወደ አካባቢው የሚገቡትስ መቼ ነው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ከዚህ ቀደም ምርጫ ቦርድ ምርጫውን አራዝማለሁ ሲል ብዙዎቻችን ስንስማማ ሕወሓት አልስማማም ብሎ የገባንበት ቀውስ ይታወሳል ብለዋል፡፡
ምን ያህል ሰው፣ ምን ያህል ሀብት እንደወደመ መገመት ትችላላችሁ ሲሉ ለተሳታፊዎች የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደመው የሰው እና ንብረትና ሀብት በትክክል ሳይገመገም እንዴት ጠፋ ሳይባል ሌላ ጥፋት ማምጣት ጥሩ አይደለም ሕዝብ ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
Comments
00:00