ታህሳስ 18፣2017
‘’በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ባለመሆናቸው አካል ጉዳተኞች በርካታ የመብት ጥሰቶች እየደረሰባቸው ነው’’ ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተናገረ።
በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ አይደሉም ተብሏል።
ይህ የተባለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባዘጋጀው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ባላቸው የተደራሽነት ሁኔታ ዙሪያ ያተኮረ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ላይ ነው።
በከተማዋ የሚገኙ ህንፃዎች አካል ጉዳተኞችን ባማከለ መልኩ የተገነቡ ባለመሆናቸው በተለይ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ አካል ጉዳተኞች በእጅጉ እንደሚገላቱ እና የመብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው አካል ጉዳተኞቹ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ሰምተናል።
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ በከተማዋ የሚገኙ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እና ምቹ አለመሆናቸውን ተከትሎ በሚደርስባቸው የመብት ጥሰት በተለያዩ ጊዜያቶች በርካታ ቅሬታ እና አቤቱታዎች ይደርሱናል ብለዋል።
አያይዘውም አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ዜጋ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ እንዳይሳተፉ እና እኩል የአገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ይላሉ።
ፍቅሩ አምባቸው ያሰናዳውን በምህረት ስዩም
Comments