በአካቶ ትምህርት ስርዓት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዳለባቸው ችግር ተለይተው እንደማንኛውም ሰው የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ቢባልም ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ግን ጎዶሎዎች እንዳሉባቸው ይናገራሉ፡፡
በልዩ ፍላጎት የሰለጠነ በቂ መምህራን አለመኖር፣ የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት ምቹ አለመሆንን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች እንዳሉባቸው ያነሳሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴርም በበኩሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው ለዚህ ደግሞ እንደ እኩዮቻቸው የትምህርት እድል እንዲያገኙ የአካቶ ትምህርት ሥርዓትን ዘርግቼ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
በተለይ የአካቶ ትምህርት ትግበራ ሲታሰብ የቁሳቁስ እጥረት፣ የሰለጠኑ መምህራን አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት ምቹ አለመሆን በዋናነት የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ችግሮች በሙሉ ለመሙላት የሚያስችል በቂ የገንዘብ አቅም የለኝም ብሏል፡፡
ተማሪዎቹ ያሉባቸውን ችግሮች በአንዴ መሙላት ባልችል እንኳን የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን እየመረጥኩ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁስ እያሟላሁ ነው ሲል ነግሮናል፡፡
የሚመረጡት ትምህርት ቤቶችም ላይ በቂ ገንዘብ እንደሚመደብ ያነሳው መስሪያ ቤቱ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት፣ ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ ምቹ እንዲሆን አድርጎ መገንባትን ጨምሮ ሌሎች ስራዎች ይከወንባቸዋል ብሏል፡፡
ነገር ግን አጠቃላይ በኢትዮጵያ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ስራዎችን ለመስራት የገንዘብ እጥረት ስለሚጋጥም የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን በመምረጥ የአካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከል እንዲሆኑ እየተደረገ ነው መባሉን ሰምተናል፡፡
Comments