00:00
ነሐሴ 15፣2016
በትግራይ ክልል ያሉ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ለፀጥታ ችግር ስጋት እንዳይፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በወቅታዊ የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳይ እና ተፈናቃዮችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ፖለቲካዊ የሀሳብ ልዩነቶች ጤናማ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ጠቅሰው ለፀጥታ ችግር ምክንያት እንዳይሆን ግን እየሰራን ነው ማለታቸውን ትግራይ ቲቪ ዘግቧል፡፡
የሀሳብ ልዩነቶች ያሏቸው ፖለቲከኞችም ልብ ገዝተው ልዩነቶቻቸውን በፖለቲካዊ አግባብ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፀጥታ አካላትም በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ሆነው ለህዝብ ደህንነት እንዲቆሙ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
የሀሳብ ልዩነቶች የተንፀባረቁበትና በመቀሌ ከተማ የተካሄዱ የተለያዩ ጉባኤተኞችም በሰላም አንዲጠናቀቁ ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል ላሏቸው ህግ አስከባሪ አካላትም ምስጋና ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡
አያይዘው ተፈናቃዮችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ተፈናቃዮች በተመለሱባቸው አካባቢዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እና የሚያስተዳድራቸውን አካል በነፃነት እንዲመርጡ ለማስቻል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
Comments
00:00