00:00
የካቲት 26 2017
ገዢው ፓርቲ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የታችኛው መዋቅር ላይ ጣልቃ እየገባ ነው ሲል ኢዜማ ከሰሰ፡፡
ፓርቲው ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ማጠናቀቁን ተከትሎ ትናንት የካቲት 25 ቀን 2017ዓ.ም ባወጣው መግለጫው ገዢው የብልፅግና ፓርቲ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ ለ3 ቀናት ባካሄደው የስራ አስፈፃሚ ኮሚት ስብሰባ በፓርቲው አሠራር ሒደት፣ በወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በቀጣይ ስለሚኖሩ ድርጅታዊ ተግባራት ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችም ማሳለፉን የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል አብረሃም በርታ(ዶ/ር) ነግረውናል፡፡
በውይይቱ ከተነሱ ሃሳቦች መካከል እተካሄደ የሚገኘው ሃገራዊ ምክክር አንዱ ነው ያሉን ሃላፊው እንደ ሀገር አላግባቡ ያሉ ችግሮቻችን የሚፈቱት በንግግር ነው ብለን ስለምናምን ነው ኮሚሽኑን የምንደግፈው ብለዋል፡፡
ነገር ግን ገዢው ፓርቲ በተለይ በታችኛው መዋቅር ባሉ የምክክር ሂደቶች የራሱን ሰዎች በማስገባት፤ የራሱን የሆኑ አጀንዳዎች እንዲቀርቡ እያደረገ በመሆኑ የኮሚሽኑ ተአማኒነት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ስለሚችል ከዚህ ድርጊቱ ሊቆጠብ ይገባል፤ ይህ ችግር በአዲስ አበባ፣በኦሮሚያና በደቡብ በነበረው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ታይቷል ይላሉ ዶ/ር አብርሃም፡፡
Comments
00:00