00:00
ሚያዝያ 22 2017
የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ ሆነዋል ሲል ኢሰማኮ ተናገረ፡፡
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን እንዲሁም እስከ 35 በመቶ የደረሰው ከደሞዝ ላይ የሚቆረጠው ግብር እንዲቀንስ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በተዋረድ ያሉ የስራ ሃላፊዎችን ቢጠይቅም እስካሁን ሁነኛ ምላሽ እንዳላገኘ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮምፌደራሽን (ኢሰማኮ) ተናግሯል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ኢሰማኮ ከ1ዓመት ከ6 ወር በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ጥናት አድርገው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ሰጥተው ነበር በሏል ኮንፌደሬሽኑ፡፡
ጥናት እንዲከወን አቅጣጫ ቢሰጥም፤ ምላሽ ባለማግኘታችን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በድጋሚ በደብዳቤ ለመጠየቅ ተገድደናል ሲል ባሳለፍነው ጥቅምት ወር 2017ዓ.ም ማለትም ከ6 ወራት በፊት ኮንፌደሬሽኑ ተናግሮ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ጥያቄዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነት እንዳገኙ የሚጠቅሱት የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤በስም ያልጠቀሷቸውን ጥናቱን ከውኑ የተባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ከምን ደረሰ ብለን በተደጋጋሚ ደጅ ብንጠናም ምናሽ አጥተናል ይላሉ፡፡
Comments
00:00