ሐምሌ 23፣2016
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ዲግሪ በማሳተም ለተማሪዎቻቸው መስጠት አይችሉም ተባለ፡፡
በግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሩ ተማሪዎች ዲግሪ የሚታተምላቸው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ይህንን ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ(ፕ/ር) ናቸው፡፡
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ #የግል_ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ዲግሪ በራሳቸው ማተም እንዲያቆሙ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎቹን ዲግሪ የማተም ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ፕ/ር ብርሀኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ‘’ሰኪውሪቲይ ፕሪንቲንግ’’ ብለው የጠሩት አዲስ የዲግሪ ህትመት አሰራር ይጀመራል ብለዋል፡፡
ይህም በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሩ ተማሪዎች ዲግሪን የማተም ስልጣን ለት/ት ሚኒስቴር ብቻ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
#ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎቹን ዲግሪ የሚያትመው ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ውጤት እና ተቋማቱ ለትምህርት ሚኒስቴር በላኩት የመረጃ ቋት(HEMIS) ተምርኩዞ እንደሆነም ሚኒስትሩ ሲናገሩ ሰምተናቸዋል፡፡
የትምህርት ተቋማቱ ላስተማሯቸው ተማሪዎች ለሚታተምላቸው ዲግሪ ህትመት ለትምህርት ሚኒስቴር ክፍያ ይፈፀማሉም ተብሏል፡፡
ይህ አሰራርም ተግባራዊ የሚደረገውም፤ በሀገሪቱ የሚታየው የሀሰት ዲግሪ(ፎርጅድ) ህትመት ለማስቆም ተብሎ እንደሆነ የትምህርት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በየኔነህ ሲሳይ
Comments