''እኔ ግን ከፖለቲካ ህይወት የወጣሁት በ2002 ዓ.ም ነው''
TRACK

''እኔ ግን ከፖለቲካ ህይወት የወጣሁት በ2002 ዓ.ም ነው''

00:00

የካቲት 25 2017

የሰብአዊ መብቶችን መንግስት ለማፈን ስላሰበ ነው የቀድሞ የኢህአዴግ ከፍተኛ ሹም የነበሩትን አቶ ብርሃኑ አዴሎን ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጎ የሾማቸው እየተባለ የሚቀርበው ክስ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ተሿሚው ተናገሩ፡፡

ከመንግስት ጫና ቢያጋጥምዎት ምን ያደርጋሉ? ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ ሲመልሱም ጫና ያሳደረብኝን አካል በግልፅ ስሙን ጭምር በመጥቀስ ለህዝብ ይፋ አድርጌ ስራዬን እለቃለሁ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

ባለፈው የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው አቶ ብርሃኑ አዴሎ አንዳንዶች መንግስት የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ተሻሽሎ ከነበረበት ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ እና ለማፈን እንዲመቸው ነው አቶ ብርሃኑ አዴሎን የሾማቸው እየተባለ የሚቀርበው ቅሬታ ልክ አይደለም ሲሉ አዲሱ ኮሚሽነር ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ለኢሰመኮ ኮሚሽነር ተደርገው ባለፈው የተሾሙት ገለልተኛ አይደሉም ከመንግስት ጋርም ግንኙነት አላቸው እየተባለ ይነገራል፤ እኔ ግን ከፖለቲካ ህይወት የወጣሁት በ2002 ዓ.ም ነው ሲሉ አቶ ብርሃኑ አዴሎ ነግረውናል፡፡

የቀድሞ ስራዬን እየጠቀሱ እና ሰነዶችን እየተመለከቱ እሱ እኮ የኢህአደግ ስራ አስፈጻሚ አባል ነበር እያሉ ሲከሱኝ እሰማለው እኔ ግን የፖለቲካ ስራ ትቼ ከ2007 ጀምሮ በጥብቅና እና በማማከር ስራ ላይ ነበርኩ ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡

ፖለቲካን የህይወት የመጨረሻም መጀመሪያም አድርጎ መሄድ አዕምሮንም ጤናንም ይጎዳል ለዚህም እኔ ፖለቲካ ህይወት ምዕራፍን ከተውኩ ቆይቻለው ብለዋል፡፡

Comments

00:00