ለተቀጣሪ ሠራተኞች የላይኛው ጣሪያ ተብሎ የሚከፈለው 10,900 ብር ደመወዝ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ፣ የዝቅተኛው ሰራተኛ መነሻ ክፍያ መሆን ነበረበት ተባለ
ሰኔ 6 2017
ለተቀጣሪ ሠራተኞች የላይኛው ጣሪያ ተብሎ የሚከፈለው 10,900 ብር ደመወዝ አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ፣ የዝቅተኛው ሰራተኛ መነሻ ክፍያ መሆን ነበረበት ተባለ።
ግብራቸውን በአግባቡ የማይከፍሉ ብዙ በመሆናቸውና የግብር አሰባሰቡም ዝቅተኛ በመሆኑ መንግስት በሚፈልገው ልክ በሠራተኛ የገቢ ግብር ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ይቸገራል ተብሏል።
ለዘጠኝ ዓመት የቆየውን የገቢ ግብር አዋጅ ይተካል ተብሎ በተሰናዳው ረቂቅ መሠረት፤ ከግብር ነፃ የሚደረግ የሰራተኛ ደመወዝ አሁን ካለበት 600 ብር ወደ 2000 ብር ከፍ እንዲል ታስቧል።
በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው #የገቢ_ግብር ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱ ድርሻው 6.8 በመቶ ብቻ መሆኑን ያነሱት በገንዘብ ሚኒስቴር የታክሲ ፖሊሲ መምሪያ ሀላፊው አቶ ሙላይ ወልዱ፣ ይህንን ማሻሻያ ማድረግ ብቻውን የሚሰበሰበው ግብር በቢሊየን ብር እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ትልቅ ማሻሻያ ለማድረግ መንግስት ይቸገራል ሲሉ ተናግረዋል።
የገቢ ግብር አዋጁ ረቂቅ ለውይይት በቀረበበት ዝግጅት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የውጭ እና ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው አቶ አያሌው አህመድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራውን ሰራተኛ እያገኘ ያለውን አነስተኛ ክፍያ አንስተዋል።
ኢኮኖሚውን እያንቀሳቀሰ ያለው ሰራተኛ እየተከፈለው ያለው ደመወዝ በወር ከ1300 ያለበለጠ እንደሆነ አንስተው ይህ ወደ ዶላር ሲቀየር በወር 7 ዶላር ከ50 ሳንቲም ብቻ ነው ብለዋል።
Comments