ሚያዝያ 17 2017
እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ዜጎችን ከአካባቢያቸው ያፈናቀለ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የሚጥስ ነው የሚል ትችት፤ ከምክር ቤት አባል ቀረበበት፡፡
መንግስት በበኩሉ የኮሪደር ልማቱ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እና ፍትሃዊነት ያረጋገጠ ነው ብሏል፡፡
ትችቱ የቀረበው የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ9 ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤት አባሉ አበባው ደስአለው(ዶ/ር) የኮሪደር ልማቱ ከሰብአዊ ተቋማትም፣ ከሚዲያዎችም፣ ከማህበረሰቡም፣ ቅሬታ እየቀረበበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለማሳያም ባለፈው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ የኮሪደር ልማቱ ሲተገበር የሰብአዊ መብቶች መጣሳቸውን ሪፖርቶች እንደሚሳዩ ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡
ለማሳያም ከልማት ተነሺዎች ጋር በቂ ምክክር አልተደረገም፣ ለተነሺዎችም በቂ ካሣ እና ምትክ አልተሰጣቸውም፣ ተነሺዎቹ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉም አስቀድሞ የፅሁፍ ማስጠንቀቅያ እንዳልተሰጣቸው ሪፖርቱን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር መወከላቸውን የተናገሩ አቡኔ አለም የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፤ ከማህበረሰቡ እና ከሰብአዊ ተቋማት በኮሪደር ልማቱ ላይ ቅሬታ እየቀረበ ነው የሚለውን ሃሳብ እንደማይቀበሉ ተናግረው፤ እንዲያውም ማህበረሰቡ እየጠየቀ ያለው መቼ ነው ሁሉም ጋር የሚደርሰው? የሚለውን ነው ብለዋል፡፡
Comments