የካቲት 13፣2016
በሽታ አምጭ ተህዋስያንን ለመለየት፣ ምርምር እና ጥናት ለማድረግ እና ክትባቶችን ለመፍጠር ያግዛል የተባለ የላቦራቶሪ አገልግሎት ስራ መጀመሩ ተነገረ፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ሲሰራ የቆየ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ዛሬ አገልግሎቱ ወደ ስራ መግባቱን ተመልክተናል፡፡
ተቋሙ የዘረመል ምርመራን ከዚህ ቀደም ሲሰራ እንዳልነበር የተናገሩት የኢንስቲትቱ ምክትል ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ተላላፊ በሽታዎች በአንድ ላይ የሚመረምር ላቦራቶሪ እና የዘረመል ምርመራን ያካተተ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
መደሃኒቶችን የተላመዱ ተህዋስያንንም በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አገልግሎት እንደሆነ ዶክተር ጌታቸው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
አዳዲስ ግንቶችን የሚሰራ፣ ተህዋስያን ላይ ምርምር የሚያደርግ አለፍ ሲልም ለበሽታ አምጭ ተህዋስያን ክትባት ለማገኘት ጭምር የሚረዳ አገልግሎት እንደሆነ የተናገሩት የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ራጃህ አቡበከር ለአገልግሎቱ የሚውሉ ማሽኖች ዘመናዊ መሆንን ጨምሮ በዚሁ ዘርፍ የተማረ ሰው ሀይል መኖሩን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ ለማስጀመርም ከሁለት ዓመት በላይ እንደወሰደ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ከዚህ ቀደም ይህ መሳዩ የተሟላ አገልግሎት በኢትዮጵያ አለመኖሩን የተናገሩት ዶ/ር ራጃህ ተላላፊ በሽታዎች ሲከሰቱ እና በሽታዎቹን ያመጧቸውን እያንዳኑዱን ተህዋስያንን መለየት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ሌሎች ሀገራት ሲኬድ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ራጃህ አሁን ወደ ስራ የገባው የላቦራሪ አገልግሎት እነዚህነ ችግሮች ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ተናግረዋል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments