መጋቢት 23፣2016
የኢትየጵያ መንግስት፤ የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ አለመፍቀዱ ሰራተኞቹ ህብረት ፈጥረው መብታቸውን እንዳያስከብሩ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በአለም ስራ ድርጅት በኩል የወጣውን አለም አቀፍ ስምምነትን በሚቃረን መንገድ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጇ የመንግስት ሰራተኞች ተደራጅተው ስለመብታቸው እንዳይጠይቁ መከልከሏ ተነግሯል፡፡
ይህም ለወራት ደመወዝ ያልደረሳቸውን ጨምሮ፣ በከፍተኛ የገቢ ግብር እና በመሰል ችግሮች የሚንገላታው የመንግስት ሰራተኛ ተደራጅቶ እና ህብረት ፈጥሮ ስለ መብቱ እንዳይከራከር እንዳደረገው ተጠቅሷል፡፡
ይህንን ለሸገር የነገረው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን(ኢሰማኮ) ነው፡፡
በኢትዮጵያ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ፤ የመንግስት ሰራተኞች የመደራጀት መብት ስለሌላቸውና የማህበሩ አባል መሆን ስለማይችሉ፤ ሰራተኞቹ ስለሚደርስባቸው የመብት ጥሰት መከራከርም ሆነ መታገል አልቻልንም ሲሉ የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚደንት ካሳሁን ፎሎ ለሸገር አስረድተዋል፡፡
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት ሰራተኞቹ እንዲደራጁ ይከልክል እንጂ፤ ይህንን የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ የሚፈቅደውና በዓለም ስራ ድርጅት በኩል የተደነገገውን ስምምነት ኢትዮጵያ ፈርማለች፡፡
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 13 መሰረት ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸው ሰነዶችና ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ አካል ሆነው እንደሚቆጠሩ ይደነግጋል፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት፤ የመንግስት ሰራተኞችን እንዳይደራጁ የከለከሉት ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን ያሰናዳውን በምህረት ስዩም
Comments