መጋቢት 18፣2016
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚኖረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ 70 ደሴቶች እንደሚፈጠሩ ተነገረ፡፡
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ፤ የተለያዩ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በግድቡ ዙሪያ የተንጣለለው ዉሃ 246 ኪሎ ሜትር የሚሆን ቦታ የሚሸፍን ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንደሚፈጥርም ተጠቅሷል፡፡
ይህም የጣና ሀይቅን በ 3 እጥፍ እንደሚበልጥ መገመቱን ተነግሯል፡፡
ይህንን አልምቶ በብርቱ ከተሰራበት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የቱሪስት መስህቦች መካከል ተጠቃሽ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡
ይህንን የነገሩን የህዳሴ ግድብ የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
በግድቡ ዙሪያ የሚጠራቀመው ውሃ እየሰፋ ሲሄድ ደሴቶች እየተፈጠሩ ነው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ በቁጥርም ሰባ ያህላሉ ተብሏል፡፡
በሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ለመጓጓዣነት የሚያገለግሉ ብዙ ጀልባዎችም ያስፈልጋሉ መባሉንም ሰምተናል፡፡
በሀይቁ የአሳ እርባታ መጀመሩንና ወደፊትም ለብዙዎች የገቢና የስራ እድል ፈጣሪነቱ የበዛ እንደሆነም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተውናል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የግድቡ የግንባታ ግብዓቶች በጊዜው ወደ ቦታው እንዳይደርሱ እንቅፋ እየፈጠሩ እንደሆነም ዶ/ር አረጋዊ ጠቅሰዋል፡፡
የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ፤ የህዳሴ ግድብ የተጀመረበት 13ኛ ዓመትን የፊታችን መጋቢት 24 ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
በሚኖረው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም፤ 700,000,000 ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል መባሉንም ሰምተናል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን ��ሰናዳውን በያሬድ እንዳሻው
Comments