መጋቢት 12፣2016 - የገበያ ቅኝት
የምርት መጠናቸው ቀንሷል፣ ከገበያ ጠፍተዋል የተባሉ ምርቶች ላይ መንግስት ድጎማ ማድረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
መንግስት ድጎማ አድርጎ ከሚያቀርባቸው መሰረታዊ ምርቶች መካከል ዘይት እና ስኳር ይገኙበታል።
ድጎማ ተደርጎበት በመንግስት ተቋማት በኩል ስለሚቀርበው ስኳር ባዛሬው የገበያ ውሎአችን ተመልክተነዋል።
የፍላጎቱን ያህል የማይመረተውን እና ከውጪም የሚገባው ስኳርን መንግስት በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ እያደረገ ቢሆንም ምርቱ ወሩን ጠብቆ አለመምጣቱ፣ ከሁለት ወራት በፊትም የ30 ብር ጭማሬ ማሳየቱ ህብረተሰቡን ፈትኖታል።
ስኳር አምራች ፋብሪካዎችን ማስፋት ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንዲኖር ከምሰራቸው ስራዎች መካከል መሆኑን እወቁልኝ የሚለው መንግስት ፋብሪካዎቹን በተያዘላቸው ጊዜ መገንባት አልቻለም፣የተገነቡትም ቢሆን የታሰበውን ያህል ሊያመርቱ አልቻሉም፡፡
በመንግስት የሚቀርበው እና የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የሚሸጠው ስኳር በከተማዋ ያሉ ነጋዴዎች በሱቆቻቸው ላይ ሲሸጡ ይታያል። ለዚያውም በ120 እና 130 ብር።
በመንግስት ድጎማ ተደርጎበት የሚቀርበው ስኳር ነጋዴው እጅ ገብቶ 30 እና 40 ብር ጭማሪ ተደርጎበት በአደባባይ ሲሸጥ ይታያል፡፡
ይሄው ግብይትም ከተጀመረ ከሁለት አመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም በሙከራ ደረጃ ላይ እንዳለ ሰምተናል።
ግብይቱም ህብረተሰቡ ወደ ሸማች ማህበራት መሄድ ሳይጠበቅበት ስኳሩ በየቤቱ እንዲደርስ በዘመናዊ መንገድ እየሰራ ነው የተባለው የማኪባ ጠቅላላ ንግድ ነው።
Comments