''ቤተሰባችን ጥለን ለስራ በወጣንበት እባካችሁ አትግደሉን'' ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ  የሰራተኞች ማህበር
TRACK

''ቤተሰባችን ጥለን ለስራ በወጣንበት እባካችሁ አትግደሉን'' ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር

Avatar

ሰኔ 9 2017

''ልጆቻችን፣ ቤተሰባችን ጥለን ለስራ በወጣንበት እባካችሁ አትግደሉን'' ሲል ጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ተማጠነ።

የተለያየ አላማ ኖሯችሁ ''በጫካ የምትገኙ ልጆቻችን ሆነ ሌሎች አካላት እኛ ለምናስተዳድራቸው ልጅ፣ ሚስት ቤተሰብ ስንል በስራ የተሰማራን ሾፌሮች አትግደሉን ሲል የሽከርካሪዎች ማህበሩ ተናግሯል።

የጉዞ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጠቅላላ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ዮሀንስ ታምራት ''የፀጥታ መደፍረስ ያሳጣን ብዙ'' ነው ሲሉ ለሸገር ራዲዮ ነግረዋል።

''እኛ ጠብመንጃ ሳይሆን መሪ ይዘን ነው የምንዞረው'' ያሉት ሀላፊው ሾፌሮች የሚያግቱ እና ጥቃት የሚያደረሱት አካላትን ተማጥነዋል።

ከማህበራቸው አባልም በጥይት ተመትቶ ጥቃት የደረሰበት እንዳለም ሊቀመንበሩ አንስተዋል።

አብዛኛው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሚከፈላቸው በተመላለሱት መጠን ስለሆነ፤ በተለይም መንገድ ተዘግቶ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ለቀናት ሲቆሙ በብዙ እንደሚጎዱ አንስተዋል።

''በሀገሪቱ ጠንካራ የሆነ ለሾፌሮች መብት የሚቆምም ሆነ የሚደግፍ ማህበር የለም'' ያሉት ሀላፊው እርሳቸው የሚመሩት ማህበር ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ የድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሚሆኑና ለብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚዳረጉ አንስተው፤ ይህ በሚገጥማቸው ወቅትም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

Comments

Avatar