የዳኞች ቁጥር ማነስን ጨምሮ የገጠሙን ችግሮችን ለመፍታት እየጣርን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተናገሩ
TRACK

የዳኞች ቁጥር ማነስን ጨምሮ የገጠሙን ችግሮችን ለመፍታት እየጣርን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተናገሩ

Avatar

የካቲት 13፣2016

የዳኞች ቁጥር ማነስን ጨምሮ የገጠሙን ችግሮችን ለመፍታት እየጣርን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተናገሩ፡፡

ፍርድ ያለተሰጠባቸው የክስ መዝገቦችን ባጠረ ጊዜ ዉሳኔ ለመስጠት የዳኞች ቁጥር ማነስ ችግር ሆኖብናል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ኤርሲኖ አቡሬ ለሸገር ነግረዋል፡፡

ክልሉ እንደ አዲስ ቢሮዎችን እያደራጀ፣ መዝገብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከሀዋሳ ወደ አዲሱ ቢሮ ሀላባ ለማጓጓዝ የወሰደባቸው ጊዜያት የፍርድ ሂደቶቹ በጊዜያቸው እንዳይታዩ ያደረጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ኤርሲኖ ተናግረዋል፡፡

የፍርድ ቤት መዝገቦቹ እልባት እንዲያገኙና ባለጉዳዮች የበለጠ እንዳይጉላሉ በክልሉ በ4 ማዕከሎች ተዘዋዋሪ ችሎቶችን በመሰየም የሰበር እና የይግባኝ መዝገቦች እየታዩ ነው ተብሏል፡፡

ተዘዋዋሪ ችሎቶቹ እየሰሩ ያሉባቸው ከተሞች ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ቡታጅራ እና ወራቤ እንደሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕ/ት አውርተውናል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ክልል በበኩሉ በክልሉ በፍርድ ሂደት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጥናት ለይቻለሁ በሏል፡፡

የዳኞች ቁጥር ማነስ የዚህኛውም ክልል ችግር እንደሆነ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቆጭቶ ገብረማርያም ነግረውናል፡፡

የዳኞች ቁጥር ማነስ የፍርድ ሂደቶችን ከማጓተቱም በላይ በሚሰጡ ፍርዶች ጥራት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕ/ት ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በየፍርድ ቤቶች የሚመደቡ የ66 ዳኞችን ሹመት አፅድቀና�� ብለውናል፡፡

ማንያዘዋል ጌታሁን ያዘጋጀውን በፋሲካ ሙሉወርቅ

Comments

Avatar