ሚያዝያ 8፣2016
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው ይመለሳሉ ቢባልም እንደታሰበው አልሆነም፡፡
ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ የድጋፍ ጥያቄ ከክልሎች ሲቀርብልኝ እሰጣለሁ፤ እያደረኩ ያለሁትም ይህንኑ ነው ብሏል፡፡
ተፈናቃዮቹ ለአራት ወራት ምንም አይነት የምግብም ሆነ ሌሎች ድጋፎች እንዳልተደረገላቸው እና በዚህም የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡
በአንድ የመጠለያ ጣቢያ ብቻ ከ 12 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ እና ከነዚህም ውስጥ አብዛኛው ህፃናት፣ አዛውንት እንዲሁም የሚያጠቡ እናቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
መንግስት ‘’የእነዚህ ተፈናቃዮች ሀላፊነት እኔ እወስዳለሁ’’ ቢልም ለተከታታይ አራት ወራቶች ግን ምንም የእህል ዘር አይተው እንደማያውቁ በሶስት የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ነግረውናል፡፡
ችግሩ ከከፋ ረሃብም አልፎ ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ቦታው ድረስ በመምጣት ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክሩም እንዳልሆነላቸው ሸገር ከተፈናቃዮች ለማወቅ ችሏል፡፡
Comments